ሲሾም
እነ ዋጥ-ሰልቅጤ እነ አግበስብስ መጥምጤን የሚያበረታታውን አባባል ታውቁታላችሁ:: "ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል::" እኔ ግን ሲሾሙ የሚያግበሰብሱና እና የሚሰለቅጡ በኋላ ቃር እንዳይሆንባቸው መጨነቅ ያለባቸው ይመስለኛል:: ታሪክም ደግሞ በሩቅም በቅርብም በስልጣን ላይ እያሉ ያለመጠን እየሰረቁ የጎሰጎሱት የግፍ እንጀራ በትግል ወይ በጊዜ ከወንበር ላይ ሲሽቀነጠሩ እንዴት እንዳቅለሸለሻቸው አሳይታናለች:: አንዳንዶች በንጹሐን ደም እየታጠቡ የተጨመላለቁ ነገስታትም የጊዜ አምላክ አሳልፎ ሲሰጣቸውና ድንገት ከከፍታቸው ሲፈጠፈጡ ደማቸው ደመ ከልብ ሁኖ መፍሰሱን ሰምተናል:: እናም ዛሬ ተገኘ ብሎ ናላ እስኪዞር ከርስ እስኪወጠር መሰርጎድ ምናልባት በኋላ ላይ ለትውከት እና ለሸርተቴ ሊዳርግ ይችላልና ተሿሚዎች የሆንን ሁሉ(እንዳንዶቻችን በራሳችን ላይና በቤት' እንዳዶቻችን በቤተ-ክርስቲያን' አንዳንዶቻችን በአገር ላይ…..ወ.ዘ.ተ.. ተሹመን ይሆናል) በመጠን ብንበላ!!
//--//
መስከረም 3 2004 ዓ.ም
እኩለ ለሊት
ሳር