Search This Blog

Thursday, June 30, 2011

ሰው ሳይጠራ ትምህርት ይጠራል?


ቅርብ ጊዜ ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ በኢትዮጵያ ስላለው የትምህርት ጥራት ችግር የሚያወራ መጣጥፍ አነበብኩ:: ለመጣጥፉ እንደ ምላሽ የተሰጡት አስተያየቶች እያንዳንዳቸው የሰጡት ምላሽ ላይ የወቀሱት አካል ወይ የነቀሱት አሰራር አለ::

በግልፅ ልንረዳው እንደምንችለው የትምህርት ጥራት ጉድለት ችግር ምንጩ አንድ ነው በሎ ማቀንቀን ሞኝነት ነው:: ምናልባት ችግሩ ላይ የሁላችንም እጅ አለበት:: ያልተነሳሳና ንፋስን መከተል በሆነ ፍልስፍና የታሰረ ትውልድና ትጋት የሌለው ማንነነት ለውጥ የማምጣት አቅም ያንሰዋል:: የትምህርት ዋንኛ አላማ ገንዘብ ማግኝት በሆነበትና ተማሪዎችና መመህራን ገንዘብ ለማግኘት የእውቀትን ጥማት አፈር ድሜ ሊያስግጡና ለወረቀት ብቻ ሊሮጡ በሚያሰፈስፉበት ድንዛዜ ውስጥ አለን::

እሺ ተጠያቂው መንግስት ነው እንበል:: መንግስት ማነው? የህዝብ የአንተ የኔ በውሸት የሚያስመርቀው ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን ስብስብ አይደለም::የኮምፒውተር መሸመቻና የ አይ ቲ ማስፋፊያውን ገንዘብ መጨፈሪያ የሚያደርገው አጎትህ አክስትህ ወይ ጎረቤትህ አይደለም?
ፍትህ ከቤት ይጀምራል:: ሰው በየራሱ ሲለውጥ ብዙ ሰዎች ይለወጣሉ:: በርግጥ አስተዳደር ላይ የተቀመጡ ሰዎች ሊያደርጉት የሚችሉትን አስተዋጽኦ መናቅ አይቻልም:: ግን ችግሩ በነዚህ አካላት ብቻ የተፈጠረ ነው ማለት እውነታውን መካድ ነው::
መምህራንም ተማሪዎችም( አብዛኞቹ) ለመማርና ለማስተማር መነሳሳት ያጥራቸዋል::
"አንድ ሻማ ከማብራት ጨለማውን እየረገሙ መኖርን"ይመርጣሉ
በዚያ ላይ መንፈስንና ሞራልን ዘንግተናል:: ስለዚህ እንደፈለግን እንሰርቃለን እንደፈለግን እንራመዳለን:: ለሀገር ያለብንን ሰዋዊ ግዴታ የምናስተውልበት ህሊናችን ሟልጯል::
ለውጡን ከራሳችን እንጀምር::እዚህ ላይ አንድ ጥቅስ ላስቀምጥ
"Education without morals would only make you a clever devil" C.S Lewis

የነጠላ ታሪክ አደጋ(The danger of ‘a’ single story)



The danger of the single story ወጣቷ ናይጀራዊት ደራሲ Chimamanda Ngozi Adichie ለአንድ ዲስኩሯ(discourse) የተጠቀመችበት ነው:: በንግግሯ ለአንድ ታሪክ መጋለጥ (ለምሳሌ አፍሪካውያን ኃላ ቀሮች ናቸው' መክሲኳውያን ስደተኖች ናቸው ..... ወዘተ) ምን ያክል ጠባብ እንደሚያደርግ የራሷንና የሌሎችን ልምድ በመጥቀስ ታስረዳለች:: ሙሉ ንግግሩን YOUTUBE ላይ ማግኘት ይችላሉ::
ታዲያ ንግግሩን ከሰማሁ በኋላ ይህ የነጠላ ታሪክ ሰለባነት በብዙ የህይወት አቅጣጫዎቻችን ችግር የሚፈጥርብን ነገር መሆኑ ከነከነኝ:: ከእግዚአብሄር ጋር ባለን ግንኙነት እናም በሙሉ ህይወታችን ስላለው ነገር ጥቂት ላውሳ::
እንዳንዶቻችን ስለ አምላክ ያለን ስዕል የፍቅር አምላክ ' የሰላም አለቃ ' የምህረት ጌታ በሚሉና በሌሎችም የቅድስናው መገለጫወች በሆኑ ቃላት ያሸበረቀ ነው:: ይህንንም ስንል ከቃሉ ከምናነበው ከህይወትም ከምንማረው ተነስተን ነውና ልክ ነን::ጥቂቶችን የቅዱሱ መጽሃፍ ቃላት ለማስቀመጥ እንኳን


"ቸር ነውና፥ ምህረቱም ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ።"ዜና16:34
"የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል"ኢሳ9:6



"ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን::" ኤፌ2:5
እናም ሁሌ ስለፍቅሩ እና ስለ ምህረቱ እናስባለን:: ጭንቅላታችን በዚህ ነጠላ ታሪክ ይሞላና ስለ እግዚአብሄር ያሉትን ተጨማሪ ነገሮች እንዘነጋለን:: ብናውቃችውም እንኳን ማሰብ አንፈለግም:: ስለ እግዚአብሄር ቅን ፈራጅነት ስለ ፍርዱም ብርታት ስለ ክንዱ ጥንካሬና ስለ ቁጣው መኣት አንናግርም:: ስለ ፍቅር በቻ ስናወራ ብንኖር ለህሊናችን ስለሚመቸን(ይህም በራሱ በጣም በጎ ነው) ይችን ነጠላ ታሪክ ይዘን እንንጦሎጦላለን:: ታዲያ ይሄ አያዋጣም:: ያኛውን አቅጣጫ ማየትና ማሳዬት ተገቢ ነው:: ሌላኝውን ታሪክ መጽሃፍ ቅዱስም መጽሃፈ-ልምድም ይደግፉታል::
"የሚያስፈራ ግን የፍርድ መጠበቅ ተቃዋሚዎችንም ሊበላ ያለው የእሳት ብርታት አለ።"ዕብ10:27
"በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነው"ዕብ10:31
እግዚአብሄር ይወዳል ስንል እግዚአብሄር ይፈርዳል ማለትን ለምን እንዘነጋለን? የነጠላ ታሪክ ሰለባዎች ነና!!
በተቃራኒው ደግሞ እግዚአብሄርን ቀጭና ተቖጪ'የሚባላ እሳት'መቀመቅ የሚያወርድ ስጋንም ነብስንም በሲኦል ሊወረውር የሚችል አምላክ ብቻ አድርገን የምናቀርብ አለን!ይህም ደሞ ሌላ በሽታ ነው::
ደሞ ባህሪን የተመለከተ የነጠላ ታሪክ ሰለባነት ላንሳ:: ሁላችንም በጣም የምንቸገርበት ነገር ይመስለኛል:: የዋህነት ብልህነት:: paradox(ይጋጬ) የሚመስል የግዜር ቃል አለ::
"እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ።" ማቲ10:16
አንዳንዶቻችን የምክሩን(dictum) አንድ ነጠላ ጫፍ ብቻ በመውሰድ እንደ እባብ ልባምነታችን በጣም እያደገ ወደ ብልጠትና ወደ ክፋት ይቀየርና የዋህነት የሚባል ነገር ከባህሪያት ታዛችን የማይገኝ ይሆናል:: የነጠላ ታሪክ(ሃሳብ) ሰለቦች እንሆናለን::
አንዳንዶቻችን ደግሞ ከህይወት መመሪያው ውስጥ "እንድ ርግብም የዋሆች ሁኑ" የሚለውን ነጥለን እንወስድና የዋህነታችን በዝቶ ማስተዋል ወደ ማጣት: ወደ ሞንኝነትና ወደ ቂላቂልነት ይለወጥብናል:: ሁለቱን ባህርያት ሁለቱን ሃሳቦች አዳቅሎ ጥሩውን ማንነት መውለድ ኤቨርስታችን ይሆናል::
እኛ ወደ አምላክ የምንሄድበትን እግዚአብሄር ወደኛ የሚመጣበትን መንገድ የሚሰራበትን ሁኔታ እንኳን በአንድ ታሪክ በአንድ አቅጣጫ ብቻ የምንወስን ጥቂት አይደለንም:: ላንዳንዶቻችን ጸሎት ድምፅን በማጉላት ላብን በማንጠፍጠፍ እጆችን በማወራጨት በመጮህና በማፏጨት ብቻ የሚደረግ ነው:: በርግጥ ይሄ ጸሎት ነው::ግን ጸሎት ይህ ብቻ አይደለም:: አንድ ሰው ድምፁን አቀስሦና አለስልሶ ስሜቱን አለዝቦ እጆቹን በደረቱ አንገቱን ከመሬቱ አድርጎ በአርምሞ አምላኩን ቢፈልግ ይህ ሰው መንፈስ የለበትም እግዚአብሄር አልነካውም ብለን መፈረጅ የለብንም::
በተገላቢጦሹ ደግሞ በጌታ ደስታ የሚዘሉትን በመንፈሱ የሚፈነጥዙትን ምን ያንቀለቅላቸዋል ምን ያቀላቸዋል አምልኮማ ተረጋግቶ ተዘምቶ(ዝም ተብሎ) ነውንጅ ብለን የምናውቃትን ታሪክ ሌሎች ላይ ልንጭን የምንሞክር እንስታለን::
ወደ ጌታ የመገስገሻ ድምጽን የመቀበያ ድምጽንም የማድረሻ መንገዶች ብዙ መሆናቸዉን መዘንጋት የለብንም:: ከአንድ መንገድ ከአንድ ታሪክ ሰለባነት መላቀቅ አለብን:: ብቻ መንገዶቹ የእወነት ይሁኑ!!
አንዳንዶቻችን እግዚአብሄር ተዓምራትን በሞቅታ በዝማሬ በእልልታ ብቻ የሚሰራ ይምስለናል:: በቃሉ ላይ ስንመሰጥ ቃሉን ስንሰማ አምላክ ጋር በጽሞና ስናወጋም እንደሚመጣ እንደሚከውን አናስተውልም:: አንድ ታሪክ አንድ መንገድ ይዘን ወይ ፍንክች ያባ ቢላዋ ልጅ እንላለን::በዚህ አቅጣጫ አንድ ቃል ላስቀምጥ::

"እርሱም፦ ውጣ፥ በተራራውም ላይ በእግዚአብሔር ፊት ቁም አለ። እነሆም፥ እግዚአብሔር አለፈ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ትልቅና ብርቱ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጠቀ ዓለቶቹንም ሰባበረ፥ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም። ከነፋሱም በኋላ የምድር መናወጥ ሆነ፥ እግዚአብሔር ግን በምድር መናወጥ ውስጥ አልነበረም።
 ከምድር መናወጥ በኋላ እሳት ሆነ፥ እግዚአብሔር ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም። ከእሳቱም በኋላ ትንሽ የዝምታ ድምፅ ሆነ።
 ኤልያስም ያን በሰማ ጊዜ ፊቱን በመጐናጸፊያው ሸፈነ፥ ወጥቶም በዋሻው ደጃፍ ቆመ። እነሆ። ኤልያስ ሆይ፥ በዚህ ምን ታደርጋለህ? የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ።"
መጽሃፈ ነገስት ቀዳማዊ 19:11-13

ወደ ፖለቲካው እንሂድ::ስለ ቴዎድሮስ 'ስለ ምኒሊክ' ስለ /ስላሴ'ስለ ደርግ' ስለ ኢህአዴግና ሰለ ተቃሚዎቹ አንድ ታሪክ ነጥለን እንይዛለን:: ያችን እየደጋገምን እሸሸው ገዳሜ እንዘፍናለን:: ቴዎድሮስ ጀግና ነው' ምኒሊክ እምዬ ናቸው' /ስላሴ ፊወዳል ናቸው' ደርግ ነቭሰ በላ ነው' ኢህአዴግ ሌባ ነው' የኢህአዴግ ተቃዋሚዎች ወሽካታ ናቸው.........ብቻ የምንመርጠውን ጥሩ ወይም መጥፎ አንድ ታሪክ መርጥን በማቀንቀን ሌላወን ሁሉ ዜማ ውበትና እውነት አልባ እናደርግዋለን:: ሁለተኛ ሶስተኛ የሚባሉ ታሪኮች አናወሳም::መካካል የሚባል ቦታ የለንም:: የመቻቻል ችሎታ(compromising) የጎደለን ስለመሆናችን ዳንኤል ክብረት "የሁለት ሀውልት ወጎች" ውስጥ በደንብ እንደፃፈ አስታውሳለሁ::በርግጥ የማናመቻምቻቸው ነገሮች እንዳሉ አንክድም::
ብቻ ስለ አንድ ነገር ወይም ስለ አንድ ሰው አንድ ታሪክ' አንድ ሃሳብ ብቻ ይዞ መሽከርከር ባለ አንድ አይናና ባለ አንድ ልቦና ሰው' ባለ አንድ ጎዳናና አማራጭ ፈርስ ያደርገናል ከነጠላ ታሪክ አምላኪነት ወጥትን እውነተኛ ይሁኑ እንጅ ሁለት ሶስት አራት ከዚያም በላይ ታሪኮችን ብንቀበልና አስፍተን ብናስብ አቻችለን ብንንኖር ምናለ?!
አስተያየቶቻችሁ ጎዶሎውን ይሞላሉ!
ክብር ለአምላካችን ይሁን:: ኢትዮጵያ ትባረክ!!!
ፀጋዬ ኃ/ ስላሴ
ዘብሄረ ሃገረ ሰማያዊ





 
ሰኔ '2003